በከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ በማድረግ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ 150 የትምህርት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በመዲናዋ የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ እንዲቻል መጠነ ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ዛሬ ተመርቀው ይፋ የሚደረጉ የትምህርት ፕሮጀክቶች የከተማ አስተዳደሩን የትምህርት የተደራሽነት አቅም ከዚህ ቀደም ከነበረው በላቀ ደረጃ የሚያሳድጉ ናቸው፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩ እያደረገው ከሚገኘው የመማሪያ ማስተማሪያ ግብዓቶች አቅርቦትና ከምገባ መርሀ ግብር በተጨማሪ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማቶችን በበቂ ደረጃ ማደራጃት እና ለመማር መስተማር ስራዉ ዝግጁ ማድረግ መቻሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ከፍተኛ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸዉን የሚያሳይ ነው፡፡
በአለም ተወዳዳሪ ሀገርና ትውልድ ለመፍጠር የሚቻለው በትምህርት ዘርፉ ላይ በሚደረገው ርብርብ በመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ በ11ዱም ክፍለ ከተማዎች 150 የትምህርት ፕሮጀክቶች በዛሬው እለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል::
ከነዚህ ውስጥም በጥራት የተሰሩ 14 አዳዲስ ትምህር ትቤቶች፣ 64 ነባር ትምህርት ቤቶች ላይ በማስፋፋያ ስራ የተገነቡ 1,655 የመማሪያ ክፍሎች፣ የአይሲቲ ክፍሎች፣ ቤተ ሙከራዎች፣ የመመገቢያ አዳራሾች፣ ቤተ መፅሀፍቶች፣ የስፖርት ሜዳዎች፣ ምድረ ጊቢዎችን ፅዱና ዉብ የማድረግ ስራ፣ የመጸዳጃ ቤቶች እና የውሃ አገልግሎትን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እና መምህራን ምቹ የማድረግ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ሲል የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።