"የፍትሕ ተቋማትን የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ


ባህር ዳር - የለውጡ መንግስት በአንድ ጊዜ በርካታ ሪፎርሞችን በመፈፀም ላይ ይገኛል; ከያዝናቸው በርካታ የሪፎርም ዘርፎች አንዱ ደግሞ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ነው ሲሉ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

ዛሬ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባስመረቃቸው ፕሮጀክቶች ዕለት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ;  የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የክልሉን የዳኝነት ሥርዓትና አጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓት ለማሻሻል እና ለማዘመን ያከናወናቸውን ተጨባጭ ሥራዎች  ከጀመርናቸው ሪፎርሞች አንዱ ነው ብለዋል።

በዳኝነት እና በፍትሕ ዘርፍ በተሰሩ የሪፎርም ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች ቢኖሩም ያልተሻገርናቸው ብዙ የፍትህ አገልግሎት ጥያቄዎች አሁንም  መኖራቸውን ተናግረው ለዚህም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በፌደራልና በክልል የፍትሕ አካላት እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል፡፡  

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ያስመረቃቸው ፕሮጀክቶችም የዚህ ሀገራዊ ዕቅድ አካል የሆኑና ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ተቃኝቶ የተዘጋጀ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውጤቶች ናቸውም ብለዋል፡፡

"የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የፍርድቤቱ አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም የክልሉ መንግሥት በአንድ በኩል ሰላምን እያፀናችሁ በሌላ በኩል ለተቋም ግንባታ ትኩረት በመስጠት በአጭር ጊዜ አስደማሚ የለውጥ ፕሮጀክቶችን በማሳካታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል" ብለዋል።