ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያን ከተሞች ለማነቃነቅ ያለመ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከተሞች 60 በመቶ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) መያዛቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከተማ ከተዘነጋ ይህን ያህል ሀብት ጥቅም ላይ እንደማይውል ተናግረዋል።
ከ50 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለው በአዲስ አበባ እንደሆነም አውስተው፣ አዲስ አበባ ላይ ካልተሠራ ይህን ኢኮኖሚ መጠቀም እንደማይቻል ገልጸዋል።
"ከተማን ማነቃነቅ አጠቃላይ ሀብታችንን ማነቃነቅ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ እስከ አሁን አዲስ አበባ ላይ በተሠራው ሥራ ምንም ብድር እንዳልተወሰደም ጠቁመዋል።
ከተማ በራሱ ገቢ ራሱን ሲቀይር እንደ ቀላል መታየት እንደሌለበት ጠቅሰው፣ "አሁን ላይ ያለውን ለውጥ ሳይ እንዴት እዚህ ቆሻሻ ውስጥ እንደኖር ይገርመኛል" ብለዋል በንግግራቸው።
ትችት ላይ ያተኮሩ ሰዎች ለራሳቸው ከቆሻሻ ርቀው፤ ሌላው ሕዝብ ቆሻሻ ውስጥ እንዲኖር የሚያስቡ ሰዎች እንደሆኑ ተናግረዋል።
ይህን የአዲስ አበባ ለውጥ ሌሎችም ሊተገብሩት እንደሚገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ጅማ፣ ጎንደር እና ባሕር ዳርን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል።