በበጀት ዓመቱ 8.2 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ ገቢ ተገኝቷል


በ2017 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ገቢ 5.1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እሰከ አሁን ባለው ሂደት 8.2 ቢሊዮን ዶላር ማሳካት መቻሉን  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡:

ይህ አፈፃፀም በ2016 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ3 እጥፍ ጭማሪ እንዳለው አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በሪሚታንስ 7 ቢሊዬን ዶላር የደረሰ ሲሆን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ቢሊዬን ዶላር እንዲሁም ከአገልግሎት 8 ነጥብ 2 ቢሊዬን ዶላር እንደተገኘ ገልፀዋል። 

ይህም ባለፈው ዓመት ከሁሉም የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምንጮች የነበረው ግኝት 24 ቢሊዬን ዶላር እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ገልጸዋል።

ዘንድሮ ከአጠቃላይ የወጪ ንግድና የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምንጭ 32 ቢሊዬን ዶላር ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

ይህ ውጤት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ስኬት መመዝገቡን የሚያመላክት ሲሆን በዘርፉ የተከናወነው ሪፎርም ውጤት ማምጣቱን በተግባር የሚያረጋግጥ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለፁት በ6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ42ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ነው፡፡