የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አሕመድ ትግራይን በሚመለከት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ሀሳብ ላይ ተመስርቶ ከህወሓት የተሰጠ መግለጫ

ዋና ቤት ፅህፈት ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሓ.ት)
=========

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አሕመድ ሰኔ 26 2017 ዓ.ም በስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ አርባ ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ ከብዙ በጥቂቱ የፕሪቶሪያ ስምምነት የተፈረመበትን ሁኔታ እንዲሁም በስምምነቱ የተገኙ ልምዶችና ውጤቶች አብራርተዋል። 

በተጨማሪም በትግራይ በኩል በተሳሳተ ስሌትና ሌሎች አገራትን በመተማመን ወደ ጦርነት የመመለስ ፍላጎት እንዳለ ገልጸው የትግራይ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻል መሆኑን በማመላከት የሀይማኖት አባቶች፣ ኤምባሲዎች፣ ሙሁራንና ባለሀብቶች ጦርነትን በማስቀረት ረገድ ሀላፊነታቸው እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከዚህ በመነሳትም ህወሓት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አሕመድ ባቀረብዋቸው ሀሳቦች ላይ ጥቅል ማብራርያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ይህንን መግለጫ አውጥቷል።

1.- የፕሪቶሪያ ስምምነት በሁለቱም ፈራሚ አካላትና በዓለማቀፍ ማሕበረ-ሰብ አስፈላጊነቱ ታምኖበት የተፈረመ ውል ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩትም ገደብ የለሽ ተጨማሪ እልቂትን ያስቀረ፣ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተስፋን የጫረ፣ ቀድሞውንም ቢሆን መቋረጥ ያልነበረባቸው የመንግስት አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ያስቻለ፣ ከነ ብዙ ጉድለቶቹ የክልላችን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ዕድል የፈጠረ ነው። 

እነዚህ ውጤቶች እንዳሉ ሆነው ስምምነቱ የህዝቡን ጊዚያዊ ችግሮች በከፊል ከማቃለል አልፎ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚያስችሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ውጤት እያመጣ አይደለም። 

የፕሪቶሪያ ስምምነት
ሕገ መንግስታዊ መርሆች እንዲጠበቁ፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ልዩነቶች በፖለቲካዊ ውይይት በዘላቂነት እንዲፈቱ፣ የህዝቡን ደህንነት እንዲረጋገጥ፣ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ፍትሕንና ተጠያቂነትን እንዲረጋገጥ፣ የወደመው ማሕበረ-ኢኮኖሚ የማገገምና መልሶ ግንባታ ሥራ እንዲካሄድ ወዘተ. የሚሉ መሰረታዊ መርሆችና  አላማዎች የተደነገጉበት መሆኑ ይታወቃል:: 

ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት እነዚህ የዘላቂ ሰላም ምሶሶዎች  እንዲሳኩ ሀላፊነቱን በቅንነት እየተወጣ አይደለም። እስከአሁን ድረስ ሕገ መንግስቱን በመጣስ ትግራይን የወረሩ ሀይሎችና በህዝቡ ላይ የተጫኑ አስተዳደሮች እንዲሁም አዲስ ሰፋሪዎች እንዲወጡ ባለመደረጉና ከቃል ያለፈ ተግባር ባለመኖሩ የተፈናቀሉና የተሰደዱ በሚልዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ወደ ቀያቸው አልተመለሱም።

በመሆኑም አሁንም የትግራይ ህዝብ ከቀየው ተፈናቅሎና ተሰዶ፣ ሕገ መንግስታዊ ልዓላዊነቱ ተቀምቶ፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ተጥሰው፣ ደሕንነቱ አደጋ ላይ ወድቆ፣ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሕገ-መንግስታዊ መብቱ ተከልክሎ፣ ለተፈጸመበት ጄኖሳይድ ፍትሕ አጥቶ፤ በድምሩ በአገሪቱ ገደብ የለሽ መድልዎና መገለል እየተፈጸመበት እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። የትግራይ ህዝብ ካሳና መልሶ ግንባታ እንጂ በደልና የጦርነት ማስፈራሪያ የሚገባው አይደለም።

2. በጦርነቱ ጊዜና ከዚያ በኋላ የተፈጠሩ በትግራይ ህዝብ ላይ የተጫኑ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም የትግራይ ህዝብና ኣመራሮቹ በሰላም ስምምነቱ ተስፋ ባለመቁረጥ እነዚህ የቆዩና አዳዲስ ችግሮች በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እንዲፈቱ የአፍሪካ ሕብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት ከፍተኛ ፓነል ስብሰባ እንዲጠራ ባይሳካም ተደጋጋሚ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፤ ይህ ጥረት ለወደፊቱም ተጠናክሮ ይቀጥላል። 

ሆኖም ግን የፌደራል መንግስት ፖለቲካዊ ውይይት በመጀመር የቆዩ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ በአፋርና በምዕራብ ትግራይ በኩል ታጣቂዎችን በማሰልጠንና
በመደገፍ፣ ወደ ትግራይ የሚገባ ነዳጅ በከፍተኛ መጠን ገደብ በማድረግ የክልሉ ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ክፉኛ በመጉዳት፥ እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በብሔራዊ ማንነታቸው ተለይተው እንዲታሰሩና እንዲሳደዱ በማድረግ እንዲሁም በትግራይ ተቋማትንና አመራሮች ላይ የተቀናጀ ጥላሸት የመቀባት ዘመቻ በማካሄድ ለሰላም ሂደቱ ዕንቅፋት በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ተጠምዷል። ይህ ሁሉ ጫና ባለበት ሁኔታ በትግራይ በኩል ለሁሉም ነገር በትዕግስት በማለፍ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ያለሰለሰ ጥረት ከማድረግ አልተቆጠብንም።

3. የሰላም ስምምነቱ ኣፈፃፅመ እጅግ የተጓተተና ስምምነቱን በግልፅ የሚጥሱ ችግሮችና ፈተናዎች ቢበዙም አሁንም በትግራይ በኩል ምንም ዓይነት የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ዝግጅት የለም። ጥያቄያችን የፕሪቶሪያው ስምምነት ይተግበር የሚል ነው፡፡
 
ጥያቄያችን በስምምነቱ መሰረት ተፈናቃዮችን ስደተኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቀያቸው ይመለሱ፣ የትግራይ ልዓላዊነት በህገ-መንግስቱ መሰረት ሙሉ በሙሉ ይረጋገጥ ነው፡፡ ይህንን ማለታችን ለዘላቂ ሰላም ያለን ቁርጠኝነት እንጂ ጦርነት ናፋቂነትን በፍፁም ሊያሳይ ኣይችልም፡፡ የትግራይ ህዝብም ሆነ የአመራሩ ፍላጎትና ተስፋ የቆዩም ሆኑ አዳዲስ ችግሮችና ልዩነቶች ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀራረብ በውይይት መፈታት የሚችሉ ናቸው የሚል ነው። 

በመሆኑም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አሕመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ችግሩ በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ እንደሚችል የሰጡትን ቃል እንዲሁም የሀይማኖት አባቶች፣ ኤምባሲዎች፣ ሙሁራንና ባለሀብቶች ጦርነት እንዳይኖር በሰላም ሂደቱ ሀላፊነታችውን እንዲወጡ ያቀረቡት ጥሪ በትግራይ በኩል ያለው ከፍተኛ የሰላም ፍላጎት ለመረዳት ጠቃሚ በመሆኑ ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። 

ይህ እንዳለ ሆኖ የአፍሪካ ሕብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት ከፍተኛ ፓነል የሰላም ሂደቱ ያለበትን ሁኔታ ገምግሞ ወደ ፊት ለመራመድ የሚያስችል አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ አሁንም ደግመን እንጠይቃለን።

4. የትግራይ ህዝብ፣ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር፣ ህወሓትና የትግራይ የጸጥታ አካላት ከሰላማዊ መንገድ ውጭ የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ምንም ዓይነት ዝግጅት እንደሌላቸው ለማረጋገጥ የአፍሪካ ሕብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት ከፍተኛ ፓነል የአፈጻጸም ክትትልና ማረጋገጫ ቡድን፣ አለማቀፍ ማሕበረ-ሰብና የዲፕሎማሲ ተቋማት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ሙሁራንና ባለሀብቶች መሬት ላይ በመውረድ እውነታውን ማየትና መታዘብ ይችላሉ።

በመጨረሻም በፕሪቶሪያው ስምምነት የተጀመረ የሰላም ሂደት ማጠናከር ፋይዳው በትግራይ ወይም ኢትዮጵያ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ለአከባቢው ህዝቦች በአጠቃላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን የሰላም ሂደቱን የሚቃረን ሁኔታ ሲያጋጥም ደግሞ የአከባቢው ሰላምና ፀጥታ ወደ ችግር የሚያስገባ በመሆኑ የዓለም ማሕበረ-ሰብ የሰላም ሂደቱን ውጤታማ እንዲሆን ሀላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን። 

ቀዳሚ ምርጫችን ምንግዜም ፍትህና ዘላቂ ሰላም ነው::
 

ህወሓት
ሰኔ 28 ቀን 2018 ዓመተ ምህረት